ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ የምናደርገውን አስተዋፅኦ አጠናክረን እንቀጥላለን-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ የምናደርገውን አስተዋፅኦ አጠናክረን እንቀጥላለን-ነዋሪዎች
ሮቤ፤ መጋቢት 22/2016(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ የምናደርገውን አስተዋፅኦ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረት የተቀመጠበት 13ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የ 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄዷል።
ለታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማሰባሰብ በክልል ደረጃ በተዘጋጀው የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርን የተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል።
የክልሉ ነዋሪዎች የግድቡ የመሰረተ ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ከገቢያቸው በመቀነስ በቦንድ ግዢና በስጦታ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የክልሉ የተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ህዝቡ በራሱ አቅም፣ ተነሳሽነትና ፍላጎት በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየ ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ድጋፉ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
የባሌ ሮቤ ነዋሪው አቶ መሐመድ አወል ከድር ግድቡ ህጻን አዋቂ ሳይባል ሁሉም የተረባረበበት በመሆኑ ግንባታው ውጤታማ እስኪሆን አስተዋጽኦቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በምስራቅ ቦረና ዞን የአሬሮ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሀምዛ በሬዳ በበኩሉ በቤተሰብ ደረጃ በሶስት ዙር ቦንድ እንደገዙ ገልፆ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅም የድርሻውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ተናግሯል።
የአዳማ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ሰርካለም ገነራ የህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔ ነው ብሎ የገነባው የሁሉም ሀብት ነው፤ እስከመጨረሻው ግድቡን እደግፋለሁ ብላለች''።
ከለውጡ መንግስት በኋላ የልማት ስራዎችን ተጀምረው እንደሚጨርሱ መመልከቱን የተናገረው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሚሲሬ ሞሲሳ ህዳሴ ግድቡም እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በጅማ ዞን የሶኮሩ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሪት ጫልቱ መገርሳ በሰጠችው አስተያየት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግራለች።
ለህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ የአቅማቸውን የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት የሮቤ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፈይሴ አለሙ ናቸው።
የግድቡ ግንባታ መሰረት የተጣለበት 13ኛ ዓመት ለማክበር ተሳትፎ የነበራቸው የክልሉ ነዋሪዎች ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ዕለቱን በማስመልከት የተዘጋጀውን ውድድር የተሳተፉና ውድድሩን ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች የገንዘብና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።