ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ
ሐረር ፤ መጋቢት 22/2016(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በማያ ከተማ ተካሄደ።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞንና የማያ ከተማ አስተዳደር በጋራ ያዘጋጁት ውድድር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ የሚከናወነውን ድጋፍ ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
በውድድሩም ከምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ከማያ ከተማ የተወጣጡ ከ10ሺ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን በስነ-ስርዓቱ ላይ የዞኑና የከተማ መስተዳድሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የማያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ኢፍራህ ወዚር፤ የኢትዮዽያውያን አንድነት መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ህብረተሰቡ ላከናወነው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅትም የግድቡን ግንባታ በስኬት ለማጠናቀቅ የዞኑና የማያ ከተማ አስተዳደር ማህበረሰብ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የሩጫው ውድድር ዓላማ ህብረተሰቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ለማድረግ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ኢፍራህ ህዝቡ ግድቡ ወደ ፍጻሜው እንዲደርስ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎች የሜዲሊያና የዋንጫ ሽልማት ከዕለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር ኢፍራህ ወዚር ተበርክቶላቸዋል።
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በስጦታ ድጋፍ መደረጉም በዕለቱ ተጠቅሷል።