ቀጥታ፡

በመዲናዋ የኮሪደር ልማት ሥራ የሚፈርስ ቅርስም ሆነ የሚቀየር የአካባቢ ሥያሜ የለም - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ የመልሶ ግንባታ የኮሪደር ልማት ሥራ የሚፈርስ ቅርስም ሆነ የሚቀየር የመዲናዋ አካባቢ ሥያሜ እንደሌለ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

በአዲስ አበባ ለመልሶ ግንባታና የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ተመጣጣኝ የገንዘብና የመሬት ካሳ አቅርቦት ተዘጋጅቶ የማስተናገድ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ከንቲባዋ ገልጸዋል። 

ከንቲባዋ በመዲናዋ የተከናወኑና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የመልሶ ግንባታ ኮሪደር የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም፤ በምርጫ ወቅት አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ-አበባ ለማድረግ በተገባው ቃል መሰረት ጉልህ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግዙፍና ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

ማዘጋጃ ቤት፣ መስቀል አደባባይ፣ ወንድማማችነትና አንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም አብርሆት ቤተ መጽሐፍት፣ ፑሽኪን አደባባይ፣ ጎተራ አቃቂ ቦሌ መንገድ ግንባታ የመሰሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል። 

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስም በ5ቱ የመዲናዋ በሮች የገበያ ማዕከላትን በመገንባት የምርት አቅርቦት እንዲኖር መደረጉንና በሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችም የጋራ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ የምገባ ማዕከላትና የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ላይ ስኬታማ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የአዲስ አበባን የቱሪዝም ምቹነትና ውበት ለማሳደግም መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በመጀመሪያ ዙርም በአድዋ ድል መታሰቢያ ፒያሳ - አራት ኪሎ - ቀበና - መገናኛ፤ አራት ኪሎ - ቦሌ አየር ማረፊያ - ቦሌ ድልድይ - መገናኛ፤ ከመገናኛ  - አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል - ሲኤምሲ እንዲሁም ከሜክሲኮ - አፍሪካ ኅብረት - ሳር ቤት ወሎ ሰፈር 40 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩልም ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆኑ፣ ለአደጋና በሽታ የሚያጋልጡ አካባቢዎችን እንዲታደሱ የማድረግ የልማት ሥራን ማዕከል ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማት ሥራዎች  ለሁሉም ማኅበረሰብ ምቹ የጋራ መጠቀሚያ ከመፍጠር ያለፈ የሚቀየር የመዲናዋ የአካባቢ ስያሜ እንደሌለ ገልጸዋል።    

በኮሪደር ልማት ሥራውም ቅርሶችና መሰረተ ልማቶችን የመንከባከብ የመጠበቅና የማደስ ሥራ በማከናወን በነበሩበት እንደቀጥሉ እንደሚደረግም ተናግረዋል። 

በቅርስነት የተለዩ እንደሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሀገር ፍቅር፣ ሸዋ ሆቴል፣ ሲቲ ኮንቬንሽን፣ የኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ቤት፣ የቀድሞዎቹ ማዘጋጃና ፖስታ ቤት ታድሰው ባሉበት እንደሚቀጥሉ አንስተዋል። 

በአዲስ አበባ ለመልሶ ግንባታና የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ተመጣጣኝ የገንዘብና የመሬት ካሳ አቅርቦት ተዘጋጅቶ እየተስተናገዱ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በዚህም የኮሪደር ልማት ጥናት አማካሪዎች ከሰጡት የካሳ ምክረ ሃሳብ በተጨማሪ ነዋሪዎችን በማካተት የ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካሳ ተዘጋጅቶ በሕጋዊ ሂደት እንዲስተናገዱ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ምትክ መሬት ለሚገባቸው ዜጎችም እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ የቤት ኪራይና የእቃ የማጓጓዣ ገንዘብን ጨምሮ 8 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ቀርቦ የማስተናገድ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በክፍለ ከተማ ደረጃ የተቋቋመው የኮሪደር ልማት ክትትል ግብረ ኃይል እንዳለ ሆኖም በከተማ አስተዳደር ደረጃ ለ5ቱም የኮሪደር የልማት ተነሺዎች ቅሬታ ምላሽ የሚሰጥ ጽህፈት ቤት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በኮሪደር ልማት ሥራው በካሳ ትንታኔ፣ በምትክ መኖሪያ፣ በመሥሪያ ቤትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አቤቱታ ያለው አካል በማንኛውም ቀንና ሰዓት ቀርቦ በማመልከት ምላሽ እንደሚያገኝ አስገንዝበዋል።     

የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስር ለማስቀጠልም በድጎማ የሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እንደተፈጠረም ገልጸዋል። 

በኮሪደር ልማቱ ወቅትም የውኃ፣ መብራት፣ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መቋረጥ እንዳያጋጥም አማራጭ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ ካለዉ ስፋት አንፃር በፒያሳ፣ አራት ኪሎና ቦሌ መስመር የመንገድና የአረንጓዴ ልማት ሥራውን እስከ ግንቦት መጨረሻ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።   

የመዲናዋ ነዋሪዎችም በኃሳብ፣ በገንዘብ፣ በልዩ ልዩ ድጋፍ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም