በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በተካሄደ ኦፕሬሽን ሰላማዊ ሰዎችን በመግደልና በማገት የአካባቢውን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ በርካታ የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት ተደመሰሱ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በተካሄደ ኦፕሬሽን ሰላማዊ ሰዎችን በመግደልና በማገት የአካባቢውን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ በርካታ የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት ተደመሰሱ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ባካሄደው ኦፕሬሽን ሰላማዊ ሰዎችን በመግደልና በማገት የአካባቢውን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ በርካታ የሸኔ የሽብር ቡድን አባላትን መደምሰሱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ልዩ ቦታው ቦፋ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በየመንገዱ ተሽከርካሪዎችን እያስቆሙ በመዝረፍ፣ ሰላማዊ ሰዎችን በማገትና በመግደል የአካባቢውን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ በርካታ የሸኔ የሽብር ቡድን አባላትን ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ደምስሶ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላትን መቆጣጠሩንም ገልጿል።
የሸኔ የሽብር ቡድን ለእኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ ይጠቀምባቸው የነበሩትን የጦር መሣሪያዎች እና ጀነሬተሮች እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶች በተካሄደው ኦፕሬሽን መያዛቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።
የሸኔ የሽብር ቡድን የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎችን ከሽብር ቡድኑ በማፅዳት የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ እየተካሄደ ያለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ኅብረተሰቡ የሽብር ቡድኑ አባላትና ሴሎቻቸውን ለፀጥታ አካላት አጋልጦ አሳልፎ እየሰጠ ያለውን ተግባር የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።