ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በደቡብ ወሎ ዞን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብ ድጋፍ አደረገ

ደሴ ፤መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በደቡብ ወሎ ዞን ደጋን ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የደሴ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፉዓድ መሃመድ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ባንኩ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡


 

ድጋፉም ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደጋን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃይ ወገኖች የሚውል የምግብ እህል መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ወርም ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው፤ ቀጣይም ተመሳሳይ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ተወካይ ወይዘሮ ቤተልሔም ብርሃኑ በበኩላቸው፤በዞኑ ለሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብ፣ የህክምናና ሌሎች ድጋፎች እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ሌሎችም ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ መሃመድ እንድሪስ፤ የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል የሚያግዛቸው በመሆኑ አመስግነዋል።


 

የተደረገላቸው ድጋፍ አሁን ያለባቸውን የምግብ አቅርቦት ክፍተት እንደሚሞላላቸው የገለፁት ደግሞ  ወይዘሮ ኢሌኒ ኢብራሂም ናቸው።


 

በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓቱ ላይ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም