በባህርዳር-ጎንደር ኮማንድ ፖስት የኮማንዶና አየር ወለድ ክፍለ ጦር በፅንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በባህርዳር-ጎንደር ኮማንድ ፖስት የኮማንዶና አየር ወለድ ክፍለ ጦር በፅንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦በባህርዳር-ጎንደር ኮማንድ ፖስት የኮማንዶና አየር ወለድ ክፍለ ጦር የሰላም አማራጭን በማይከተሉ ጽንፈኞች ላይ የሚወስደውን የኃይል እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ።
ፅንፈኛው ከተሰገሰገበት መንደር የመመንጠር ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠሉንና ሌሎች የፅንፈኛው ተላላኪዎችን በሚያስተምር መንገድ ተገቢውን ቅጣት ማግኘታቸውን በባህርዳር- ጎንደር ኮማንድ ፖስት የአየር ወለድ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አየልኝ አስናቀ ተናግረዋል።
ሰሞኑን በባህር ዳርና መሸንቲ ዙሪያ በተደረገው አሰሳ የዘራፊው ቡድን አከርካሪ መመታቱን የገለፁት ሌተናል ኮሎኔል አየልኝ አስናቀ ፅንፈኛው መሸንቲ ዙሪያ ለጥፋት ተልዕኮ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ሞተር ሳይክሎች በቁጥጥር ስር አውለናል ብለዋል።

እንዲሁም በባህርዳር ዙሪያ በተደረገው ኦፕሬሽን ደግሞ ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎች፣ ተተኳሾችና ፅንፈኛው ለጥፋት ተልዕኮ ሲገለገልባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ገልጸዋል።
የኮማንዶና አየር ወለድ ክፍለ ጦር ከሰሜን ምዕራብ ዕዝ፣ከምስራቅ ዕዝና ከሌሎች አጎራባች የጦር ክፍሎች ጋር በመሆን ፅንፈኛውንና ዘራፊውን ቡድን የመደምሰስ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት በመወጣቱ በኮማንድ ፖስቱ ቀጠና በአሁኑ ሰዓት አንፃራዊ ሰላም ተገኝቷልም ብለዋል።
የዘራፊው ቡድን ስብስብ በሠራዊታችን የደረሰበትን ጥቃት መቋቋም ተሰኖታል ያሉት የአየር ወለድ ምክትል አዛዡ በመረጃና ጥናት ላይ በመመስረት ከተሰገሰጉበት ከእያንዳንዱ አካባቢ መንጥሮ የማውጣትና አስፈላጊውን ተመጣጣኝ እርምጃ የመውሰድ ዘመቻው በሚገባ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

ሌተናል ኮሎኔል አየልኝ ክፍለ ጦሩ አጠናክሮ በቀጠለው ፅንፈኛውን የመደምሰስ ዘመቻ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
እንደ አዲስ የተደራጀው የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከሠራዊታችን ጋር በቅንጅት ለመስራት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ገልፀው የክልሉን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ሠራዊቱ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው ብለዋል።