ባለፋት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት የሚያረጋግጡ ናቸው - ዶክተር ዓለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፋት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት የሚያረጋግጡ ናቸው - ዶክተር ዓለሙ ስሜ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦ ባለፋት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
የፌዴራል ተቋማት የብልጽግና ፓርቲ አባላት ማጠቃለያ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው።
በዚሁ ጊዜ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል ተቋማት የብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ ብልጽግና የዘመናት የፖለቲካ ስብራትን በዕውቀት እና በእውነት እየጠገነ ይገኛል ብለዋል።
ፓርቲው ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡ በመስራት ላይ መሆኑን ጠቁመው ሃሳብን ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድም አመርቂ ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ለሌሎች ሀገራት የዕድገት መሰረት የሆኑ ቴክኖሎጂዎች እና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በሀገር በቀል እሳቤ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተጋ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው፣ ህብረብሔራዊ መሆኑን ጠቁመው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።
ፓርቲው በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ያሉት ዶክተር አለሙ ስሜ በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ክብር፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የኢትዮጵያን ልዕልና ለድርድር እንደማያቀርብም አረጋግጠዋል።
የአይቻልምን መንፈስ በተጨባጭ ስራዎች መስበሩን ጠቁመው በግብርና፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎችም ዘርፎች አርዐያ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቁመዋል።
ፓርቲው በአመለካከት እና በተግባር ደረጃ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በድል እያለፈ መሆኑን ገልጸው ያስመዘገባቸው ስኬቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በትጋት ይሰራል ብለዋል።
የፓርቲው አባላት በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ጠንካራ ፓርቲ እውን እንዲሆን መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ባለፋት ጊዜያት የተመዘገቡ ስኬቶች የብልጽግናን አይቀሬነት የሚረጋግጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የህዝቡን የመልማት እና የማደግ ፍላጎት ለማረጋገጥና የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ በቀጣይም በመደመር እሳቤ በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።