45ኛው የዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ ይካሄዳል

206

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦45ኛው የዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ በሰርቢያ ቤልግሬድ ይደረጋል። 

በሻምፒዮናው ላይ ከ51 አገራት የተወጣጡ 485 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።

በዚህ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ14 ሴትና በ14 ወንድ በአጠቃላይ በ28 አትሌቶች እንደምትወከል ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 


 

በሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት አትሌቶችን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ልምምዳቸውን አድርገዋል።

አትሌቶቹ በሦስት ዙር ተከፍለው ሰርቢያ ከገቡ በኋላ ትናንት ልምምዳቸውን ማከናወናቸውንና ሁሉም ተወዳዳሪዎች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶችና ሴቶች፣ ከ20 ዓመት በታች ወንዶች በ8 ኪሎ ሜትር፣ ከ20 በታች ሴቶች በስድስት ኪሎ ሜትርና 4 በ 2 ኪሎ ሜትር የድብልቅ ዱላ ቅብብል (ሴትና ወንድ) በሻምፒዮናው የሚካሄዱ የውድድር አይነቶች ናቸው።

6 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ከቀኑ 7 ሰዓት፣ 8 ኪሎ ሜትር  ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ከቀኑ 7 ሰዓት ከ 35፣ 4 በ2 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ዱላ ቅብብል (ሴትና ወንድ) ከቀኑ 8 ሰዓት 15፣ 10 ኪሎ ሜትር የአዋቂ ሴቶች 8 ሰዓት ከ45 እና የ10 ኪ.ሜ. አዋቂ ወንዶች ውድድር ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ይደረጋሉ።

በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች ታደለች በቀለ፣ ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር፣ ብርቱካን ወልዴ፣ መሰረት ሲሳይ፣ በቀለች ተኩ እና መብራት ግደይ ይሳተፋሉ።

በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች በሪሁ አረጋዊ፣ ጭምዴሳ ደበሌ፣ ቦኪ ድሪባ፣ ጌታቸው ማስረሻ፣ ታደሰ ወርቁ እና ብርሃኑ ፀጉ ይወዳደራሉ። 

በ6 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመታት ሴቶች ውድድር ማርታ አለማየሁ፣ አሳየች አይቼው፣ ሮቤ ዳዲ፣ ሽቶ ጉሚ፣ የኔዋ ንብረት እና ለምለም ንብረት ኢትዮጵያውን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው። 

በ 8 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ወንዶች  ሰውመሆን አንተነህ፣ አቤል በቀለ፣ ይስማው ድሉ፣አብዲሳ ፈይሳ፣ መዝገቡ ስሜና ጀንበሩ ሲሳይ ይሳተፋሉ።

4 በ 2 ኪሎ ሜትር የድብልቅ ዱላ ቅብብል (ሴትና ወንድ) ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 አገራት ይሳተፋሉ።

በዱላ ቅብብሉ ላይ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁለት ወንድና ሴት አትሌቶችን ታሳትፋለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም