በአማራ ክልል ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ከ32 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ከ32 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
ባህርዳር ፤መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦- በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ32 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የህዝብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በክልሉ በተለያየ ዓይነት 35 ቢሊዮን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ መደረጉን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።
የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተናኘ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በበጀት ዓመቱ በቦንድ ግዥ 70 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
ከዚህም ባለፉት ስምንት ወራት በተደረገው ጥረት ከ32 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
በቦንድ ግዥ የተሰበሰበው ይሄው ገንዘበ ከመንግስት ሰራተኛው፣ ከባለሃብቱና ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከአርሶ አደሩ፣ ከሌላውም የህብረተሰብ ክፍልና ከተለያዩ ተቋማት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ግድቡን ለመጠበቅ በዘንድሮው የበጋ ወቅት በተካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ 30 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት ስራም ተከናውኗል ብለዋል።
በክልሉ በቀሪ ወራት በዕቅድ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ከፍያለው ማለፉ በሰጠው አስተያየት፤ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጊዜ ጀምሮ 30 ሺህ ብር የሚጠጋ የቦንድ ግዥ በመፈፀም አሻራውን እንዳስቀመጠ ተናግሯል።
በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ተጨማሪ የ20 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት እንደሚደግፍ ነው የገለፀው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት የሆነው የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብርሃን የሚያገኙበት ጊዜ እንደተቃረበ በቅርቡ ይፋ ከተደረገው የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም መረዳት እንደቻለም ጠቅሷል።
ወጣቱ የጀመረውን ጥረት በማጠናከር ታሪክ የመስራት ኃላፊነቱን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፏል።
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥና በጉልበቱ ባደረገው አስተዋፅኦ 35 ቢሊዮን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ ማድረጉን ከማስተባበሪው ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።