በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሰላማዊ መንገድ መታገል ለሚፈልግ የፖለቲካ ቡድን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል - አቶ ሀይሉ አዱኛ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሰላማዊ መንገድ መታገል ለሚፈልግ የፖለቲካ ቡድን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል - አቶ ሀይሉ አዱኛ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሰላማዊ መንገድ መታገል ለሚፈልግ የትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ላለው ቡድን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ተናገሩ።
የክልሉ መንግስት ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በማንኛውም ሁኔታ ለሰላማዊ ውይይትና ንግግር በሩ ክፍት መሆኑንም ገልጸዋል።
የቢሮ ሃላፊው ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፖለቲካ ረገድ የታዩ ለውጦች ላይ ያተኮረ ቆይታ ከኢዜአ ጋር አድርገዋል።
አቶ ሀይሉ እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኦሮሞን ህዝብ አጀንዳ ይዞ የሚታገል ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን የሚያቀርብበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።
በክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን ለማህብረሰብ እንዲያቀርቡ፣ ሀሳባቸውን እንዲሸጡ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም ተናግረዋል።
በዚህ ዘመን ጦር የሚያማዝዝና በመሳሪያ የሚፈታ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አለመኖሩን ያነሱት አቶ ሀይሉ፤ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ከሌሎች ጋር በእኩልነት ተጠቃሚነቱን ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል።
በእነዚህ የለውጥ ዓመታት ምቹ የመታገያ መድረክ ተፈጥሮ ሳለ የህዝቡን መሰረተ ልማት ማውደምና የህዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማወክ ተገቢነት የለውም ብለዋል።
አሸባሪው ሸኔ ግን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ወደ ጎን በመተው በክልሉ በምዕራብና በደቡብ አካባቢዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን የሽብር ቡድኑ እየሄደበት ያለው መንገድ የህዝቡን ችግር እያባባሰ መሆኑን በመረዳት ለሁለት ጊዜ የሰላም ንግግር መደረጉንም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ቡድኑ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዝግጁ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ባሳየው ግትር አቋም ምክንያት ውይይቶቹ ፍሬ ሳያፈሩ መቅረታቸውን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በመሆን ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በሚያከናውነው የህግ ማስከበር ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በተሰራው የህግ ማስከበር ስራ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፤ ሰላምን የማጽናቱ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አጽንኦት ሰጠውታል።
አቶ ሀይሉ አያይዘውም በእነዚህ የለውጥ ዓመታት የተገኙ መልካም ውጤቶችን ለማጽናት መጋቢት 24 በክልሉ ሁሉም ዞኖች ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፎች ይደረጋሉ ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ህዝቡን ለማነቃቃት በክልሉ አምስት ከተሞች መጋቢት 22 የሩጫ ውድድር የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።