ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት የኢፍጣር መርሐ ግብር በወንድም ካሊድ ምግባረ ሠናይ ፋውንዴሽን ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት የኢፍጣር መርሐ ግብር በወንድም ካሊድ ምግባረ ሠናይ ፋውንዴሽን ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት የኢፍጣር መርሐ ግብር በወንድም ካሊድ ምግባረ ሠናይ ፋውንዴሽን ተካሄደ ።
በፋውንዴሽኑ በተካሄደው የኢፍጣር መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች፣ የእምነት አባቶች፣ አማኞች፣አርቲስቶች፣በማዕከሉ ድጋፍ የሚደረግላቸውና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንደገለፁት፤ መልካም ልብ እንደ ወንድም ካሊድ ማብዛት ከቻልን ተቸግረው ጎዳና ላይ የሚወጡ ወገኖች አይኖሩም ነበር።
የጀመርነውን የአብይና የረመዳን ጾም በተጀመረው መተሳሰብና መደጋገፍ እንዲያልቅ እየታየ ያለው ኢትዮጵያዊ ባህል መሠረቱ እየተጠናከረ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን በተለይ በኃይማኖት ሳይለያዩ አብሮነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ለሌሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲበረከቱና ዜጎች ከራስ አልፈው ያላቸውን ዕውቀትና አቅም እንዲለግሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።