ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝን ተግባራዊ አደረገ

264

አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓትን በዛሬው እለት በይፋ አስጀምሯል።

ፕሮግራሙን በይፋ ያስጀመሩት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ናቸው።

ዋና ስራ አስፈፃሚው በዚህ ወቅት እንደገለጹት በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓት ኮርፖሬሽኑ በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የጀመረው ሪፎርም ውጤታማነትን የሚያሳይ ነው።

ለፕሮግራሙ አተገባበርና ስኬታማነት ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም የመሬትና መሰረተ ልማት ዘርፍ አመራሮችና ሰራተኞች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

ኮርፖሬሽኑ በዛሬው እለት ተግባራዊ ያደረገው ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓት በኮርፖሬሽኑ የሚተዳደሩ መሬቶችን በጠቅላላ መረጃቸውን ዲጂታላይዝ በሆነ መንገድ ለመያዝ፤ የሊዝና የኪራይ መረጃዎችን በዘመናዊ ሲስተም በአግባቡ መዝግቦ ለመያዝና ለመከታተል የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

በተጨማሪም ሪፖርት ለመቀበል እና አጠቃላይ ከመሬት ጋር ተያይዞ ያለውን እንቅስቃሴ በሲስተም ማከናወን እንደሚያስችልም ተነስቷል።

በፕሮግራሙ ላይ የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃላፊዎች እንዲሁም በፕሮጀክቱ ተሳታፊ የነበሩ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም