የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ማጠናከር ይገባል 

309

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

"ብክለት ይብቃ፤ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ኃሳብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆን አገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተጀምሯል።    

ንቅናቄው የአካባቢ ጥበቃ ውጤታማነትን ለማሳደግ የወጡ ሕግና ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ በዘርፉ  የባለድርሻ አካላትንና የማኅበረሰቡን ሚና ለማጠናከር ያለመ ነው።      
 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ንቅናቄውን ሲያስጀምሩ፤ የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ብክለት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።  

በዚህ መነሻነትም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የተጠናከረ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ጨምሮ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ከተሞችን ውብና ፅዱ ለማድረግ ውጤታማ ሥራዎችን እየሰራች መሆኗንም ገልፀዋል።

ከግብርና ሥራ ጋር የሚስማማ የሌማት ትሩፋት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ተግባራዊ የተደረጉ የአስተራረስ ዘዴዎችንም ጠቅሰዋል። 

የአካባቢን ብክለትና የተፈጥሮ ኃብትን ከብክነት መጠበቅ የሕልውና ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅዱና የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ንቅናቄው ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።

በመሆኑም በንቅናቄው ላይ ሁሉም የሚመለከተው አካል በንቃት መሳተፍ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ከተሞችም የሚያስወግዱትን ቆሻሻ በአግባቡ ሥርዓትን የተከተለ በማድረግ ውብና ምቹ የአኗኗር ዘይቤን መገንባት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የአየር፣ የውኃ፣ የአፈርና የድምፅ ብክለቶች ለመቀነስ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።


 

የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው ለዜጎች ምቹ ከባቢ ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ በተጀመረው ንቅናቄም በርካታ ዜጎችን በማሳተፍ የአየር፣ የአፈር የውሃና የድምፅ ብክለትን ለመከላከል ትኩረት እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የተገኙት የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመከላከል ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው በንቅናቄው የተቀመጡ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

በመድረኩ የፌደራል ተቋማት የሥራ  ኃላፊዎች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የክልል የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ  ኃላፊዎች እንዲሁም የአለም ዓቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም