የ3ኛው ትውልድ የተቋማት ሪፎርም በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት መስራት ይገባል -ከንቲባ ከድር ጁሀር

146

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው የ3ኛው ትውልድ የተቋማት ሪፎርም በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የተቋማቱ አመራሮችና ባለሞያዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የከተማዋ ከንቲባ ከድር ጁሀር አሳሰቡ።

በድሬዳዋ አስተዳደር በአዲሱ ትውልድ የሲቪል ሰርቪስ ግንባታ ፖሊሲ በሶስተኛው ትውልድ የሪፎርም ማስተግበሪያ የዝግጅት ስራዎች ላይ ውይይት ተካሒዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከንቲባ ከድር ጁሀር እንደተናገሩት የ3ኛው ትውልድ የተቋማት ሪፎርም በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት መስራት አስፈላጊ ነው።

ለዚህም የየተቋማቱ አመራሮችና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው 3ኛው ትውልድ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም መሰረት በማድረግ በአስተዳደሩም የተመረጡ 6 ተቋማት እና 1 ወረዳ ወደ ሪፎርም እንዲገቡ በማድረግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።


 

በዛሬው እለት በከንቲባ ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ከንቲባ ከድር ጁሀር እንዲሁም ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡሁ በጋራ በመሩት መድረክ የሪፎርም ማስተግበሪያ የዝግጅት ምእራፍ ስራዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም የሚመራበት 5 ዋና ዋና ተግባራት ሲሆኑ ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ግሎባላይዜሽን፣ ከባቢያዊ ሁኔታ፣ብሄራዊ አርበኝነት ለሀገራዊ ተወዳዳሪነት ሀብት መፍጠር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ እይታዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

የአስተዳደሩ የሪፎርም አስተግባሪ ተቋማቱ በዝግጅት ምዕራፍ እስከ አሁን የተሰሩ የአደረጃጀት፣ የሕግ ማዕቀፎችና የአሰራር ማንዋሎች ፣ለህዝቡ እና ለሰራተኛው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ተወያይተዋል።

በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ልየታ ስራዎችን፣ የታዩ ጥንካሬዎችን እና ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መደረጉን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም