በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

105

ሶዶ ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ህገ-ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና ከ12 ዞኖች ለተውጣጡ ፈጻሚ ባለሙያዎች በወላይታ ሶዶ ከተማ እየሰጠ ነው።


 

የቢሮው ሃላፊ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የገበያ ስርአቱን በማዛባት የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እያደረገ ነው።

ከዚህም ባለፈ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴው ህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

ገበያው እንዳይረጋጋ ምክንያት የሆኑ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ህገ-ወጥ ደላሎችን ከገበያ ስርአት ለማስወገድ ቢሮው ከፍትህ አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከፍትህ አካላት በተጨማሪ ቢሮው ከተለያዩ ባለደርሻ አካላት ጋር በመሆን የቁጥጥር ስራውን ማጠናከሩን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ በጉምሩክ ከተፈቀዱ 3 ኬላዎች ውጭ በርካታ ኬላዎች በየአካባቢው መኖራቸው ህገ-ወጥ ንግድን ከመቆጣጠር ይልቅ ምርት እንዳይንቀሳቀስ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ለማስተካከል በተደረገው ጥረት 33 ኬላዎችን ማንሳት እንደተቻለና ቀሪዎችን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ከነዳጅ ግብይት ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር በተደረገው ንቅናቄ በክልሉ ካሉ 89 ነዳጅ ማደያዎች መካከል 86ቱ በቴሌ እና ሲቢኢ ብር መገበያየት እንዲችሉ መደረጉን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ዘርፉ አሁንም ከህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች አለመጽዳቱን ጠቁመው ይህን ለማስተካከል  የዛሬው ስልጠና የተሳለጠ የገበያ ስርአት ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የሰብል ምርት ቡድን መሪ አቶ ሽፈራው ጀጉ፣ በዞኑ የሚስተዋለው ህገ-ወጥ ንግድ ገበያው እንዳይረጋጋ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

የንግድ ስርአቱ በአሰራር እንዲመራና የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ ህገወጥነትን ለመከላከል የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።

ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስቆም በዞኑ ባሉ ሁሉም ወረዳዎች ህገ-ወጥ የንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ ነው  ያሉት ደግሞ ከጋሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት የሰብል ምርት ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ዳንኤል ናቸው።


 

ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በሰብል ምርት ግብይት፣ በእንስሳትና በገበያ መሠረተ ልማት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም