በጋምቤላ ክልል አልፎ አልፎ እየተከሰተ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ አካላት ውይይት አደረጉ 

135

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል አልፎ አልፎ እየተከሰተ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በተገኙበት የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላት ውይይት አድርገዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሸነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በተካሄደው ውይይት ላይ አንዳንድ ግለሰቦች ጎራ እየለዩ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን እያደረሱ እንዳሉ በመገምገም ችግር ፈጣሪዎችን በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፀጥታ አካላት የፀጥታ ችግሩን ለመቅረፍ ወደ ኦፕሬሽን በመግባት ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር እያዋሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የፖሊስ ሠራዊቱን አባላት፣ የስደተኞች ካምፕንና በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚጠበቁ ተቋማትን ጎብኝተዋል።

ሠራዊቱ በተመደበባቸው አካባቢዎች ሁሉ እየተወጣ ያለውን ፖሊሳዊ ተልዕኮ አጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ መስጠታቸውን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም