አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከሸማቾች ጋር የሚያገናኝ  ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ 

188

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከሸማቾች ጋር የሚያገናኝ ኤግዚቢሽንና ባዛር  ተከፈተ፡፡

ኤግዚቢሽኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉና የገበያ ትስስር  እንዲፈጥሩ ታስቦ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

በለሚኩራ ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተገኝ ጓለ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አምራቾች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩና ህብረተሰቡም አማራጭ ግብይት እንዲያገኝ እንደሚያግዝ  ጠቁመዋል፡፡

መንግስት በልዩ ትኩረት አምራቾች በስራ ሂደታቸው የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ችግርና የመሰረተ ልማት ጥያቄ በመፍታት ምርታቸውን ተደራሽ እንዲያደርጉ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

እንደ ክፍለ ከተማው ነባራዊ ሁኔታ በምርት ሂደት ላይ ተግዳሮት የገጠማቸውን አምራቾች በመለየት መፍትሄ መስጠት መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፉ አምራቾች እንዳሉት ባዛሩ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ 

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አምራቾችን እርስ በእርስ ከማቀራረብ ባለፈ ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንዲጠቀም ሰፊ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል፡፡ 

በባዛሩ በቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ ኬሚካል፣ በዕደ ጥበብ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሰማሩ  አምራች ኢንዱስትሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከዛሬ ጀምሮ  እስከ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ለ5 ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።

 

 
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም