አሰባሳቢ ትርክቶችን በማጠናከር በሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር ትውልድ መገንባት ይገባል - አቶ ብናልፍ አንዱዓለም

219

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ ብዝሐነትን በአግባቡ የሚያስተናግድና አንድነትን የሚያጸና አሰባሳቢ ትርክት በማጠናከር በሀገር ብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር ትውልድ መገንባት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ ሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል "ቀጣናዊ ሰላምና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር" በሚል መሪ ሃሳብ በጋራ ያዘጋጁት የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፤ በመጠላለፍና በመጠፋፋት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል የኖረ በሽታ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለሀሳብ የበላይነት ዋጋ ከማይሰጥና ጉልበትንና ኃይልን መሰረት ካደረገ የፖለቲካ ባህል በመላቀቅ የጋራ ልማትን ለማረጋገጥና የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ከሚከፋፍሉና ከሚያራርቁ ነገሮች ይልቅ የሚያቀራርቡና የሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ የበለጠ በማተኮር የሁላችንም የጋራ ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን ማድረግ የሚቻለው ብዝሃነትን የሚያስተናግድና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰባሳቢ ትርክት በመገንባት መሆኑን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ በኩል እኔ አውቅልሃለው በሚል አስተሳሰብ የተቃኘ በሌላ በኩል ደግሞ ልዩነት ላይ ብቻ ያጠነጠነ ነጠላ ትርክት መንሰራፋቱን ገልጸው ሁለቱም አካሄድ አጥፊ መሆናቸውን አንስተዋል።

የትውልዱን አስተሳሳሪ ገመድ ወደ ጎን የገፋ ነጠላ ትርክትን በመተው ብዝሐነትን በአግባቡ የሚያስተናግድና የጋራ ማንነትን የሚያጠናክር ትርክት መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊነትን ጠንካራ የጋራ ቤት አድረጎ የሚገነባ አዲስ አሰባሳቢ ትርክት መሬት እንዲይዝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የጋራ ትርክት መገንባት ቢያንስ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ጠንካራ አገረ መንግስት መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በመሆኑም ቢያንስ በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ሚኒስትሩ እነዚህም ብሔራዊ ጥቅም፣ ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ እሴት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር ትውልድ መገንባት እንዲሁም በጋራ ማንነት እና እሴቶች ዙሪያ መግባባት መፍጠር ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ማለት ነው ብለዋል።

በዚህ መንገድ የኢትዮጵያን ቀጣይነትና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ከተሰራ በቀጣናውም ሰላምና አብሮነትን ለማጽናት አጋዥ እንደሚሆንና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ትስስርም አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም