የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቀዳሚና ተመራጭ የመረጃ ምንጭ የሚያደርጉትን አሰራሮቹን ማጠናከር አለበት

93

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቀዳሚና ተመራጭ የመረጃ ምንጭ የሚያደርጉትን አሰራሮቹን ማጠናከር አለበት ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ቦንጋ ከተማ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ ምልከታ አድርጓል።


 

በምልከታውም ኢዜአ ለዜጎች ተመራጭና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭነቱን በተሻለ ለማሳደግና የይዘት ስራዎችን በተለያዩ ቋንቋዎችም ተደራሽ በማድረግ ተመራጭና ተወዳዳሪ ሊሆን እንደሚገባውም ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።

በተለይም ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ዜጎች በሚያውቁት ቋንቋ ብዝሃነትን በጠበቀ መልኩ ተደራሽ ቢደረጉ ተመራጭነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ቋሚ ኮሚቴው ያስረዳው።

የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ቡድን አስተባባሪ አቶ ከድር እድሪስ ኢዜአ ዜና የሚያመርትበትንም ሆነ ለማህበራዊ ሚዲያ ተደራሽ የማድረግ አቅሙን ተጠቅሞ በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ስለ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በስፋት በማቀድ ዜጎች ሃገሪቱ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲያውቁ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የምርመራ ጋዜጠኝነትን ቀዳሚ የተቋሙ ተልዕኮ በማድረግ ለሙስና ትግሉ የበኩሉን ሊያበረክት ይገባል ያሉት የቡድኑ አስተባባሪ ለዚህም ከሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው ማሳሰቡን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም