ኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ምሕዳር ለመፍጠር እያደረገች ያለችው ጥረት የሚበረታታ ነው- ዓለም ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ምሕዳር ለመፍጠር እያደረገች ያለችው ጥረት የሚበረታታ ነው- ዓለም ባንክ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ምሕዳር ለመፍጠር እያደረገች ያለችው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የዓለም ባንክ የአፍሪካ ስርዓተ ፆታ ማበልጸጊያ ጥናት ቡድን መሪ ማይክል ሱልቫን ተናገሩ።
የጥናት ቡድን መሪው ማይክል ሱልቫን ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የፋይናንስ ምሕዳር አካታችነት ላይ ሰፊ ክፍተት ይታያል።
በኢትዮጵያ ያለውን የፋይናንስ አካታችነት ማሳደግ ከተቻለ እንደ ሀገር በየዓመቱ ከ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ሀገራዊ ዕድገት ማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል።
አካታች የፋይናንስ ስርዓት መረጋገጥ በራሱ በሀገራዊ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
የፋይናንስ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የሴቶች ድርሻ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የፋይናንስ አካታችነት የነፍስ ወከፍ ገቢ እድገት እንዲያስመዘግብ ከመርዳቱ ባለፈ ለዘላቂ ብልጽግና እንደሚበጅ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አካታች የፋይናንስ ምሕዳር ለመፍጠር አካታች ፋይናንስ ስትራቴጂ በመቅረጽ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።
በትናንትነው ዕለት በይፋ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሴት የፋይናንስ ባለሙያዎች ኔትወርክም አካታች የፋይናንስ ስርዓት እንዲጎለበት ስለሚያግዝ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ኔትወርኩ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት፣ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ብሎም እንደ ሀገር ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እንዲመዘገብ የራሱ ሚና እንደሚኖረውም ነው ያስረዱት።