ለቀጣናው የጋራ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክተው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ለጎረቤት አገራት ትልቅ የምስራች ነው

174

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ለቀጣናው የጋራ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክተው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሊጠናቀቅ እየተቃረበ መሆኑ ለጎረቤት አገራት ትልቅ የምስራች ነው ሲሉ የግድቡ ተደራዳሪ ቡድን አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ተናገሩ። 

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 95 በመቶ መድረሱን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

ግድቡን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር የኢትዮጵያ የተደራዳሪ ቡድኑ አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ጋር ኢዜአ ቆይታ አድርጓል። 

በዚህም በኢትዮጵያውያን እውቀትና ገንዘብ እየተገነባ ያለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱ የሚያኮራ መሆኑን ኢንጂነሩ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁ የሕዳሴ ግድብን መሥራት መጀመሯን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ግንባታውን ለማስቆም ተጽዕኖ ለማድረግ የተሞከረበትና በግድቡ ዙሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ የተጻፈበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁንና ኢትዮጵያ በእኩልነት፣ በፍትሃዊ ተጠቃሚነትና በሌሎች ላይ ጉዳት አለማድረስና አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት በተመለከተ የምታራምደው መርህ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል እንዳስቻላት ጠቁመዋል።

ይልቁንም ግድቡ የተፋሰስ አገራት ላይ ምንም ጉዳት የማያደርስ፣ የጋራ ተጠቃሚነትንና ትስስርን የሚያጠናክር እንዲሁም የጎርፍ ሥጋትን የሚቀነስና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት  አስገንዝበዋል።

ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ  ለቀጣናው የኃይል ምንጭ በመሆን የጋራ ልማት በማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው ግድቡ አሁን ላይ ሊጠናቀቅ መቃረቡ ለአፍሪካ በተለይም ለጎረቤት አገራት ትልቅ የምስራች ነው ብለዋል።

ግድቡ እዚህ እንዲደርስ አስቸጋሪውን የአየር ጸባይ ተቋቁመው ቀን ከሌት በትጋት ለሰሩ  ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበው ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ኃብት በመጠቀም የምጣኔ ኃብት እድገቷን ለማፋጠን ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንዳለባት ጠቅሰዋል።  

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ በሦስቱ አገራት መካከል በሚደረገው ድርድር በሥምምነት እንዲቋጭ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጓን አስታውሰዋል።

እንዲያም ሆኖ በግብጽ በኩል በሚቀርቡ ተገቢነት የሌላቸው ኃሳቦች ሥምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን ጠቅሰው ኢትዮጵያ አሁንም ድርድሩ በሥምምነት እንዲቋጭ ያላትን ጽኑ ፍላጎት ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም