ኢትዮጵያ በቀጣናው የጀመረችውን የኃይል ትስስር አጠናክራ ትቀጥላለች

148

 አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናው የጀመረችውን የኃይል ትስስር አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።   

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት እያቀረበች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል የበለጠ ለማስፋፋት እየሰራች ነው። 

ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ገልጸው ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል እስከ ደቡብ አፍሪካ የማድረስ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

በቅርቡም ለታንዛኒያ ኃይል ለማቅረብ ሥምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው ሌሎች የጎረቤት አገራትም ለአብነትም ደቡብ ሱዳን፣  ኡጋንዳና ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመውሰድ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል። 

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ንግግር መጀመሯን ገልጸው ኢትዮጵያ በቀጣይም በቀጣናው የጀመረችውን የኃይል ትስስር አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ያረጋገጡት።     

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ሥርቆት እየተበራከተ መሆኑን ጠቁመው ይህን ለመከላከል የኅብረተሰቡ ርብርብ ያስፈልጋል። 

የመሰረተ ልማቶች ስርቆት በኃይል የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋማት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደሚፈጥር ጠቅሰው ይህም በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ እንደሆነ ተናግረዋል።  

ለዚህም ከወረዳ እስከ ቀበሌ በሚገኙ መዋቅሮች ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በቅርቡም ኅብረተሰቡ በዚሀ ሂደት ተሳትፎውን ለማሳደግ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጀመር ጠቁመዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም