በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል - ግብርና ሚኒስቴር

254

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦  በዘንድሮው የ2016 በጀት ዓመት አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።  

በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ኃብት ልማትና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በመጪው የክረምት ወቅት 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

ይህንንም ተከትሎ እስካሁን 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ገልጸው ቀሪ ችግኞች ደግሞ  በቀጣይ ወራት ለማዘጋጀት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።  


 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከሚተከሉ ችግኞች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህም የፍራፍሬ ችግኞች፣ ለእንስሳት መኖ የሚውሉና ለአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ችግኞች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ቀሪ 40 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች የአየር ንብረት ተፅዕኖ ለመከላከል የሚረዱ የደን ዕፅዋቶች (አገር በቀል የዛፍ ችግኞች) መሆናቸውን ጠቁመዋል።  


 

የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን በበቂ ሁኔታ ከወዲሁ እየተዘጋጁ መሆኑንም ነው ያብራሩት።    

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እስካሁን ከ32 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል። 

በቀጣይ ሦስት ዓመታት ደግሞ 17 ነጥብ 5 ቢሊየን በመትከል 50 ቢሊየን ችግኞችን በስምንት ዓመታት ውስጥ ለመትከል እቅድ ተይዟል።

እስካሁን ለተተከሉት ችግኞች በተደረገው ክትትልና እንክብካቤ የችግኞቹ የጽድቀት መጠን ከ90 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።

ችግኞቹ የአየር ንብረትን ከለውጥን በመቋቋም እንዲሁም ደርቀው የነበሩ ኃይቆች ጭምር ውኃ መያዝ እንዲጀምሩ ማስቻሉን ገልጸዋል። 

መርኃ ግብሩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የአረጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ በመከላከል ለሌሎች አገራት አርአያ እንድትሆን ማስቻሉን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም