ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ደቡብ ሱዳን ለሚሰማሩ የኢትዮጵያ ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች ሽኝት ተደረገ

153

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ደቡብ ሱዳን ለሚሰማሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች ሽኝት ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በሽኝት መርሃግብሩ  ላይ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሚሰማሩ የፖሊስ መኮንኖች ባስተላፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት በሥነ-ምግባሩ እና በወታደራዊ አቅሙ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተፈላጊ እና ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡


 

በስምሪታቸው ለሚያገኟቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እና የተለያዩ ሀገራት የፖሊስ መኮንኖች የኢትዮጵያ ፖሊስ አሁን የደረሰበትን ደረጃ የሚያመላክት የላቀ ሥነ-ምግባርና ፖሊሳዊ ሙያ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ዕድሉን ሳያገኙ በጡረታ በክብር የተሰናበቱ የፖሊስ ሠራዊቱ አባላትን በቀጣይ ለማካተት እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

ለሰላም አስከባሪ ተጓዦች ተልዕኳቸው የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ኮማንደር ተገኝ አጋዥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ስምሪት ተቋርጦ እንደነበረ አንስተው ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና ማኔጅመንቱ ከፍተኛ ጥረት አድርገው እንደገና በማስጀመራቸው ላቅ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያቶች በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በአብዬ ግዛቶችና በሐይቲ የተሰማሩ የፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ አመራሮች የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት በመወጣት የሀገራቸውንና የተቋማቸውን መልካም ገፅታ መገምባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለሰላም ማስከበር የሚሰማሩ የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በሚሰማሩበት ሀገር ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ባህልና እሴት በመጠበቅና በማክበር እንደቀደመው ሁሉ የሀገራችንና የተቋማችን ስም ከፍ ብሎ እንዲነሳ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የሴት ፖሊስ ተሳታፊዎች ቁጥር እስካሁን ከነበረው የሰላም መስከበር ስምሪት በቁጥር ብልጫ ያለው እና 11 ሴት አመራሮች የሚሳተፉበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው እና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም