ኢንተርፕራይዙ ለ2016/17 የመኽር ወቅት ከ360 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እያዘጋጀ ነው

81

ሮቤ ፤መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦  የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ለ2016/17 የመኽር ወቅት ከ360 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ። 

በኢንተርፕራይዙ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አስቻለው እንደገለጹት ኢንተርፕራይዙ ለ2016/17 የመኽር ወቅት ከ17 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ምርጥ ዘር እያባዛ ነው።

በዚህም ከተሰበሰበው ምርት ላይ ከ360 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ሰብል ምርጥ ዘር አ ይነቶች እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።  

እስከ አሁን በተደረገው ጥረት 142 ሺህ ኩንታል የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ምርጥ ዘር ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚው መሰራጨት መጀመሩን ገልጸዋል። 

ከምርጥ ዘሮቹ መካከል የዋግ በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ 'መንዶዩ'፣ 'ዳካ'፣ 'ገላን'፣ 'ቡላላ' የሚባሉ የስንዴ ዝሪያዎችና ሌሎች የቢራ ገብስ እንዲሁም የባቄላ ዝርያዎች ይገኙበታል ብለዋል። 

ኢንተርፕራይዙ በመደበኛነት ከሚያካሄደው የዘር ብዜት በተጓዳኝ የእርሻ ማሳ አካባቢ የሚኖሩ አቅም ለሌላቸው ሴት አርሶ አደሮች የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።

ከኢንተርፕራይዙ ምርጥ ዘርን በሚፈልጉት መጠንና ጊዜ ስለሚያገኙ በምርታማነታቸው ላይ ከፍተኛ መሻሻል እየታየ መምጣቱን የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ገልጸዋል። 

ከሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል መሐመድ ሼህ ሁሴን፣ ''ከዚህ በፊት ምርጥ ዘር ስለማንጠቀም ከአንድ ሄክታር ከ20 ኩንታል በላይ ምርት አናገኝም ነበር'' ብለዋል። 

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ከኢንተርፕራይዙ የሚያገኙትን ምርጥ የስንዴ ዝሪያ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ከአንድ ሄክታር እስከ 55 ኩንታል ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

''ኢንተርፕራይዙ በአቅራቢያችን መሆኑ ምርጥ ዘር በምንፈልገው መጠንና ወቅት ለማግኘት የተሻለ ዕድል ፈጥሮልናል'' ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳ አርሶ አደር ጎሳ ለማ ናቸው። 

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በዞኑ የሚገኙ ሮቤና ሲናና እርሻዎችንና በምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሄራሮ፣ ሁንጤና ቢሊቶ ሲራሮ የሚባሉ እርሻዎች እንዳሉት ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም