ፓርቲው ያጋጠሙትን ፈተናዎችና ጫናዎች በፅናት በማለፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድል እያስመዘገበ ነው -አቶ ሽመልስ አብዲሳ

167

አዳማ፣መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፡- ብልጽግና ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል ያጋጠሙትን ፈተናዎችና ጫናዎች በፅናት በማለፍ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድል እያስመዘገበ መሆኑን የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

''ቃል በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና'' በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የፓርቲው ኮንፈረንስ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ፓርቲው ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን የሚያስችል መሰረት የተጣለበት ተግባር አከናውኗል።

ፓርቲው ሀገሪቷ ከነበረችበት ችግሮች እንድትወጣ በሙሉ አቅሙ በመስራት በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ድል እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።


 

''በድርብ ፈተናዎችና ጫናዎች ተስፋ ሳንቆርጥ መላው ህዝቡንና አባላቱን በማሰባሰብ አሁን ያለንበትን ድል አስመዝግበናል'' ያሉት አቶ ሽመልስ ኮንፈረንሱ ያሉትን ችግሮች በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል።

በቀጣይ ሁሉት ዓመት ተኩል የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅዶችን በአግባቡ በመለየት በጥራትና በፍጥነት መፈፀም እንደሚገባም አስረድተዋል።

ብልሹ አሰራር፣ ሌብነትና ህገ ወጥ ተግባራትን በማረምና ስርዓት በማስያዝ የብልጽግና ጉዞን በአንድነት ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

መላውን የክልሉን ህዝብ በማንቀሳቀስ ለተሻለ ድል አባላቱና አመራሩ በሙሉ አቅሙ መረባረብ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው ፓርቲው ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በማንገብ አመርቂ ድል እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲው ሀገራዊ ማንነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ያደረገ የጋራ ትርክት ለመገንባት በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በመጀመሪያው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የተቀመጡትን አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊ መደረጉን አስታውስዋል።

በዚህም በምግብ ራስን ለመቻል፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በጥራትና በብዛት በማምራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ሰላምን ማጽናት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ ጽንፈኝነትን ለማስወገድ በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።

ኮንፈረንሱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም