የብልጽግና ፓርቲ ከቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጋር ስትራተጂካዊ አጋርነቱን ይቀጥላል - አቶ አዲሱ አረጋ

195

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2016(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ ከቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጋር ያለውን ስትራተጂካዊ አጋርነት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ህዝብ እና አለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

በአቶ አዲሱ አረጋ የሚመራ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የተካተቱበት ልዑክ ቻይና ቤጂንግ ገብቷል።

ጉብኝቱን አስመልክቶ አቶ አዲሱ ለኢዜአ እንደገለጹት የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲና ብልጽግና ፓርቲ ስትራተጂካዊ አጋርነትና ወዳጅነትን የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ከተለያዩ የፓርቲው አመራሮች ጋር ውይይት ይደረጋል።


 

የፓርቲ ግንባታ፣ በህዝባዊ ንቅናቄ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ፣ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጉዳዮች የልምድ ልውውጡ ዋና ዋና ጭብጦች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተያዘው መርሀ ግብር መሰረትም በቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ አመራሮች ለቡድኑ ገለፃ መደረግ ተጀምሯል።

የቻይናን ብልፅግና ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ብዝሀዊ ማንነትን ሳይበርዙ እድገትን እውን ለማድረግ የተሄደበት ርቀት፣ከሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብ የሆነ የዲፕሎማሲ መርህ ያስገኘው ፍሬ በገለፃው ተካቷል።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ዘመናትን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የገነባች መሆኗንና ፓርቲውም ይህ ግንኙነት ወደ ተሻለ ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የልኡካን ቡድኑ ቆይታም ከዚህ በፊት በፓርቲ ለፓርቲም ሆነ በመንግስታዊ ደረጃ በስልጠናና በተሞክሮ ልውውጥ ተባብሮ ለመስራት ከስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች በፍጥነት እየተተገበሩ ስለመሆናቸው አመላካች መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም