በጋምቤላ ክልል በመኸር እርሻ ከ164 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል

86

ጋምቤላ፤ መጋቢት 19/2016 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ለመኸር እርሻ ከ164 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑም የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስተወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሎዋል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2016 /17 የምርት ዘመን ተግባራዊ መሆን የጀመረውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ስኬታማ ማድረግ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው።

የመኸር ግብርና ልማቱን በመካናይዜሽን፣ በምርጥ ዘርና በሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂ ግብዓቶች በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጠናከር የድጋፍና የክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች 48 አዳዲስና ነባር የእርሻ ትራክተሮች በማሰማራት ለማሳ ዝግጅቱ ግብዓት እንዲሆኑ ስምሪት መደረጉንም ተናግረዋል።


 

በምርት ዘመኑ ከ164 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት የተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ መጣሉን ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ ለማልማት የታቀደው መሬት ከቀዳሚው ዓመት በ13 ሺህ ሄክታር፣ በምርት ደግሞ በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለውም አስረድተዋል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽኑ በምርታማነት አዋጭነታቸው የተለዩ አምስት ሺህ ኩንታል የበቆሎ፣ የሩዝ፣ ስንዴ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች የምርጥ ዘር ግብዓቶችን የማሰራጨት ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

የግብርና ልማቱን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳዳግም አርሶ አደሮችን በየአካባቢቸው ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም ኃላፊው አስረድተዋል።


 

የትራክተር ስምሪት ከተደረገባቸው ወረዳዎች መካከል የጎደሬ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኩምቱ ቶው በሰጡት አስተያየት፤ ለ2016/17 የመኸር ግብርና ልማት የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በስፋት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ባለፈው ዓመት ድጋፍ የተደረጉላቸውን ትራክተሮች ወደ ስራ በማስገበት ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች አስፈላጊው የማሳ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ “አዲስ ድጋፍ የተደረጉት ትራክቶች ለመኸር እርሻው ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥሩ ናቸው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም