ከልዩነት ይልቅ አንድ የሚያደርጉ መሰረቶች የበለጠ እንዲጎለብቱ የሃይማኖት ተቋማት ሚና የላቀ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

196

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ)፡- ከልዩነት ይልቅ አንድ የሚያደርጉ መሰረቶች የበለጠ እንዲጎለብቱ  የሃይማኖት ተቋማት በትኩረት በመስራት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የዐቢይ እና የረመዳን አጽዋማትን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የጋራ የጸሎትና አፍጥር መርሃ ግብር  በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።  


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።  

በመርሃ ግብሩ ላይ ለሀገር ሰላምና አንድነት ጸሎት ተደርጓል።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ ፍቅርን፣ አንድነትና  አብሮነትን የበለጠ ለማጠናከር ታልሞ የተዘጋጀ ነው።  

ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን መሰረቶች ይበዛሉ ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ አነዚህን መሰረቶች ይበልጥ ማስፋት እና ማጎልበት ይገባል ብለዋል። 

ቤተ እምነቶች ስለ ሰላምና ፍቅር በመስበክ ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁንም አንድ የሚያደርጉ መሰረቶችን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።  

በአዲስ አበባ ሰላምን፣ ልማትንና የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው ለዚህም በጋራ መስራታችን  የጎላ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።

ይህንን በማጠናከር በቀጣይም በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም