በባህር ዳር  ከተማ  የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶችን ለማሳካት የመንግስት ሰራተኛው ሊረባረብ  ይገባል 

179

ባህር ዳር፤ መጋቢት 19 / 2016 (ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር  የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶችን ለማሳካት የመንግስት ሰራተኛው ግንባር ቀደም ሆኖ ሊረባረብ እንደሚገባ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አሳሰቡ።

አስተዳደሩ ከመንግስት ሰራተኞች ጋር በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይቷል።

ምክትል ከንቲባው  አስሜ ብርሌ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ  የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሁሉንም አካላት ያልተቆጠበ ርብርብና ዕገዛ ያስፈልጋል።

ባለፉት ስምንት ወራት በህብረተሰበቡ ተሳትፎ ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠን የሚያግዙ የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል። 

እንዲሁም  ካለፈው ዓመት ከተሻገሩ  በተጨማሪ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ አዳዲስ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።


 

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የስራ እድል የማመቻቸት ተግባር ማከናወን እንደተቻለም አብራርተዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቀጣይነት ለመቅረፍም ችግሮቹ ተለይተው ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

የመንግስት ሰራተኛውም የተገኘውን ሰላም አፅንቶ ከማዝለቅ ጎን ለጎን የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በቀሪ ወራት ለመፈፀም ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤ የሆኑ ብልሹ አስራሮችን የመንግስት ሰራተኛው በመታገልና በማጋለጥ ህብረተሰብ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።


 

ከውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል  አቶ ታዬ መላኩ በሰጡት አስተያየት፤  ብልሹ አሰራርን በመታገል ህብረተሰቡ የሚፈልገውን የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

''የተቀጠርነው ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ነው ፤ ሁላችንም ሚናችን በመገንዘብ ባለጉዳይን ሳናጉላላ  ታማኝ ሆነን ልናገለግል ይገባል'' ብለዋል።

በመድረኩም የክልልና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችና የባህር ዳር ከተማ የመንግስት ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም