በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሚመራው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ ቀጥሏል - የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ

172

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሚመራው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ተጠናክሮ መቀጠሉን ፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከጥር 29 እስከ አሁን በቀጠለው ኦፕሬሽን በቁጥጥር ሥር በዋሉ ተጠርጣሪዎች ላይ 2 ሺህ 7 መቶ 63 የምርመራ መዝገብ ማደራጀቱን አስታውቋል።

ፖሊስ ቀደም ሲል በኦፕሬሽኑ የተገኙ ስኬቶችን በየጊዜው እየገመገመ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ በገባው ቃል መሠረት ያካሄደውን የተቀናጀ ኦፕሬሽን ውጤት፦


 

1. በእገታ፣ በዘረፋ እና በተለያዩ የማጭበረበር ወንጀሎች የተሳተፉና የተለያዩ 16 የወንጀል ዓይነቶችን የፈፀሙ በአንድ ቡድን የተደራጁ 12 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ጉዳዩን አስመልክቶ ፖሊስ የምርመራ ውጤቱን በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦

2. የወንጀል ተግባር ሲፈፀምባቸው የተያዙ 20 ተሸከርካሪዎችና ሁለት ሞተር ሳይክሎች፣

3. 58 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ509 መሰል ጥይቶች ጋር፡

4. 67 የተለያዩ ሽጉጦች ከ 427 መሰል ጥይቶች፣ በርካታ የኤፍ ዋን ቦንብ (F1 bomb) ስብርባሪ እና ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎች፣

5. የተሰረቁ 66 ላፕቶፕ፣ 28 ታብሌት፣ 2 ሺህ 9 መቶ 86 የተለያዩ የሞባይል ስልኮች፣ ለሕገ-ወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 103 ሲም ካርዶች፣

6. የተሰረቁ በርካታ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች፣

7. የተለያዩ ኢንች ያላቸው 23 ቴሌቪዥኖች፣ የኤሌክትሪክ ገመዶች እና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣

8. በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 5 ሚሊየን ብር እና 3 ሺህ 5 መቶ የአሜሪካን ዶላርን ጨምሮ የ15 ሀገራት ልዩ ልዩ ገንዘቦች፣

9. በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናት፣

10. 208 ሚሊየን ብር ግምት ዋጋ ያላቸው በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር የገቡ መድኃኒቶች፣

11. ለወንጀል መንስኤ የሆኑ 2 ሺህ 4 የሺሻ እቃዎች እና የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች በተካሄደው ኦፕሬሽን ተይዘው ታዛቢዎች በተገኙበት እንዲቃጠሉ ተደርጓልም ብሏል።


 

አሁን ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ መሆኑን የገለፀው ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጁ ወንጀሎችን በተቀናጀ ኦፕሬሽን መቆጣጠር የሚያስችል ስምሪት ተጠናክሮ የቀጠለ እና በቀጣይም በሀገራችን የሚካሄዱ ሕዝባዊ፣ መንግስታዊ እና ሀይማኖታዊ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት አድርጎ የተጠናከረ ጥበቃ ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ አረጋግጧል።

ኅብረተሰቡም እንደተለመደው ሁሉ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፌዴራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

ንብረት የተወሰደባችሁ ግለሰቦች በአቅራቢያችሁ በሚገኝ ፖሊስ መምሪያ ማስረጃ እያቀረባችሁ ንብረታችሁን እንድትወስዱ ሲል ጥሪ ማቅረቡን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም