ቀጥታ፡

በክልሉ በሦስት ወራት ውስጥ ለሕዳሴው ግድብ 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዷል -ጽህፈት ቤቱ

አርባ ምንጭ ፤ መጋቢት 19/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሦስት ወራት ውስጥ ለሕዳሴው ግድብ 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱን በክልሉ የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገራዊ አንድነትን ከመፍጠር ባለፈ እንደሀገር የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት መሆኑም ተመላክቷል።

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ በክልሉ የሕዳሴው ግድብ ድጋፍ አሰባሰብ ሥራንና ቀጣይ ተግባራት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ መክሯል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሚልኪያስ እስራኤል እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሀገሪቱን የሃይል አቅርቦት ያሳድጋል።

ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ ከመሆን ባለፈ ብሔራዊ መግባባት የፈጠረ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ሚልኪያስ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ ባለፉት ስምንት ወራት በተደረገው ጥረት ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

በቀጣይ ሦስት ወራትም ህብረተሰቡን በማስተባበርና የተለያዩ የገቢ አማራጮችን በመጠቀም 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

በክልሉ በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች በህዝባዊ ንቅናቄ ገቢ የማሰባሰብ ሥራው ዛሬ መጀመሩን የገለጹት ሃላፊው፣ ህዝቡም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ በርገኔ በቀለ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ያስተሳሰረ የዚህ ትውልድ አድዋ ነው ብለዋል።


 

የጋሞ ዞን ህዝብ ባለፉት 13 ዓመታት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፣ ቀሪ የግንባታ ሥራውን ለማጠናቀቅ በሚደረጉ ድጋፎችም የድርሻውን እንዲወጣ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ መግባባት ከመፍጠር ባለፈ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሃይል የሚያስተሳስር ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ መሰለ መስፍን ናቸው።


 

ከሃይል አቅርቦት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፣ የግድቡ ቀሪ የግንባታ ሥራው እንዲጠናቀቅ በቦንድ ግዥ፣ በ8100-A እንዲሁም በሌሎች አማራጮች ህዝቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር የማስተባበር ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ የሕዳሴው ግድብ የግንባታ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ669 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም