ኢዜአ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያደርገውን ሙያዊ እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያደርገውን ሙያዊ እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
ኢዜአ ከፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በምስል እና ድምጽ ቀረጻ ላይ ሲሰጥ የነበረው ሙያዊ ስልጠና ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ፤ ተቋሙ በሚዲያ ዘርፍ ያለውን የረጅም ዓመት ልምድና ተሞክሮ የማካፈል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተለይም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ሙያዊ አቅም በማጎልበት ረገድ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሰልጣኞቹ በምስልና ድምጽ ቀረጻ ላይ የተሰጣቸው ስልጠና፤ መረጃዎችን በቀላሉ ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛቸዋል ብለዋል።
ስልጠናውን የተከታተሉ ባለሙያዎች በበኩላቸው በዘርፉ ያላቸውን እውቀት እና ክህሎት ማጎልበት የሚያስችል ስልጠና ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ከሰልጣኞቹ መካከል ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የመጡት አቶ ምስጋናው ተስፋዬ ስልጠናው የነበራቸውን ክህሎት ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የተቋማቸውን ዓላማ ለማሳካት እና ልምዳቸውን ለስራ ባልደረቦቻቸው ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ኮከቤ ቢፍቱ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በምስል እና ድምጽ ቀረጻ ላይ ክህሎት እንዳልነበራቸው በመጥቀስ ከስልጠናው ብዙ ስራዎችን መስራት የሚያስችል አቅም ማጎልበታቸውን ተናግረዋል።
ሰልጣኞቹ በኢዜአ የተሰጣቸው ስልጠና በቀጣይ የተሻለ የህዝብ ግንኙነት ስራ ለመስራት አዎንታዊ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።