ኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ምሕዳር ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች ነው- ብሔራዊ ባንክ ገዥ

178

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ምሕዳር ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የሴቶችን ፋይናንስ ተጠቃሚነትና አመራርነት ለማሳደግ ያለመ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ (ኒውፊን) በይፋ ተመስርቷል።

የኒውፊን መመስረትም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ሂደት ሴቶች የራሳቸው ድርሻ እንዲያበረክቱ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑ ተነስቷል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ በፋይናንስ ዘርፉ በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለው የተሳትፎና የተጠቃሚነት ድርሻ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ዘላቂነትና መተማመን ያለበት የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባትም ባንኮችን ጨምሮ በፋይናንስ ዘርፉ የሴቶች ተካታችነት መረጋገጥ እንደሚገባው ተናግረዋል።

በፋይናንስ ተቋማት ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣትም በአገር አቀፍ ደረጃ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በሀገራዊ ኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

የሴቶችን አካታችነት ክፍተት ለማጥበብ ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ ገቢራዊ መደረግ የጀመረ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂው ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሴቶች የፋይናንስ አካታችነትን ከግብ ለማድረስ የኔትዎርኩ መመሥረት ትልቅ አስቻይ አደረጃጀት እንደሆነም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካይ ዳይሬክተር ዱዩና ፔትረስኩ፤ ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ የወሰደቻቸውን ፖሊሲ መር ማሻሻያዎች አድንቀዋል።


 

ለአብነትም ባንኮችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረግ፣ የባንኮች ተቀማጭ ፈንድ ማቋቋም እና አካታች የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት ብሄራዊ ባንክ ያደረጋቸውን ጥረቶች ጠቅሰዋል።

በሁሉም መስክ ያሉ አመረታዎች በቂ ባለመሆናቸው የጾታ እኩልነት እና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ግድ ይላል ብለዋል።

በዚህም ሰፊ ክስተት የሚስተዋልብትን የሴቶች የአመራርነት እና አገልግሎት የማግኘት ምጣኔ በመቅረፍ እርምጃዎች መጠናከር እንዳለባቸው ገልፀዋል።

የዓለም ባንክ የሴቶችን አካታች የፋይናንስ ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን እና ሴቶች በአመራርነት እና በፈጠራ ተጠቃሚነታችው እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።

ባንኮችን ጨምሮ በሁሉም የፋይናንስ ዘርፎች ያሉ ሴቶች አደረጃጀታቸውን በማጠናከር በፋይናንስ ምህዳሩ የሴቶች ተሳትፎ በተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የኔትወርኩ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የዘምዘም ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መሊካ በድሪ፤ በፋይናንስ ተቋማት የሴቶች አመራርነት ተሳትፎ ከ12 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም የሴቶችን የአመራርነትና የፋይናንስ አካታችነት ለማጠናከር ፖሊሲ አቀፍ በሆነ ተግባራዊ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የፋይናንስ ተቋማት ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልፀው፤ ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ ሴቶችን በቦርድ አባልነት ያቀፈው ኔትወርኩም በሁሉን አቀፍ ሴቶች አካታችነት የራሱን ሚና ይወጣል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም