በኢትዮጵያ ለ31 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ተሰጠ

105

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ለ31 ሆቴሎች ከአንድ እስከ አራት የኮከብ ደረጃ ተሰጣቸው።

በ2014/15 በጀት ዓመት በ64 ሆቴሎች ላይ በተደረገ የአስገዳጅ መስፈርት የሆቴሎች ምዘና ተደርጎ 31 መስፈርቱን አሟልተው ተገኝተዋል።

በዛሬው እለትም የሆቴሎቹ የኮከብ ደረጃ በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጓል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ በሆቴሎች መካከል ጤናማ ፋክክር እንዲኖር፣ ደረጃውን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠትና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።


 

የሆቴል ምደባው አለም አቀፍ ተሞክሮን የቀመረና 12 መስፈርቶችን የያዘ ሲሆን ውስጣዊና ውጫዊ ገፅታ፣ መታጠቢያ፣ የመኝታና የማብሰያ ቦታዎች፣ የደህንነት ጥንቃቄ እና ሌሎችንም ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሆቴሎች ላይ በተደረገው ምዘና አብዛኞቹ ሆቴሎች አስገዳጅ ደረጃን ያላሟሉ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በዚህም በ64 ሆቴሎች ላይ ባደረገው ምዘና 31 ብቻ አስገዳጅ መስፈርቱን በማሟላት ከአንድ እስከ አራት የኮከብ ደረጃን አግኝተዋል።

በዚህም 7 ሆቴሎች ባለ አራት ኮከብ፣ 9 ሆቴሎች ባለ ሶስት፣ 5 ሆቴሎች ባለ ሁለት እንዲሁም 8 ሆቴሎች ባለ አንድ ኮከብ ደረጃ የተሰጣቸው ሲሆን የሁለቱ ምደባ በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የዛሬዎቹን ጨምሮ እስካሁን 369 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃዎችን ማግኘታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም