በኢትዮጵያ ስኬታማ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመረጃ ማዕከል መሠረተ-ልማት ተገንብቷል - ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና

260

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የዕውቀት ሽግግር የተገኘበት ስኬታማ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመረጃ ማዕከል መሠረተ-ልማት መገንባቱን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥነ-ምህዳር ግንባታ ላይ የሚመክር አውደ-ጥናት አካሂዷል። 


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የቴክኖሎጂ ልማት ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ሙያተኞች ተሳትፎ ለዘመናዊ ሁሉን አቀፍ የዜጎች አገልግሎት ፍላጎት መሳለጥ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የዕውቀት ሽግግር የተገኘበት ስኬታማ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመረጃ ማዕከል መሠረተ- ልማት መገንባቱን ጠቁመው፤ ለዘርፉ ልማትም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና አላቸው ብለዋል።

ለአብነትም የግብርና፣ ጤና፣ የፋይናንስ እና መሰል ተቋማትን የሥራ አቅምና ምርታማነት በሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተሰራባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የአስተዳደር ውጤታማነትን ለማሳደግም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመረጃ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከተሞች በስማርት ሲቲ ግንባታ ሂደት ላይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የቴክኖሎጂ ሥርዓት የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መስክ ብቁ የሰው ኃይል እንዲኖር ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ትምህርት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። 

ከዚህ ጎን ለጎንም እስከ 15 ቴታ ባይት መሸከም የሚችሉ ግዙፍ የመረጃ ማዕከል በመገንባት የዘርፉ ተመራማሪ ሙያተኞች ክህሎታቸውን የሚያበለጽጉበት የሥራ ክፍል እንደተዘጋጀ ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቢቂላ ተክሉ፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ብዝኃ መስኮችን የሚነካ ዘርፍ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ክህሎት ልማት እየሰራን ነው ብለዋል።


 

ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር መሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት በመውሰድ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥነ-ምህዳር ግንባታ የአውደ-ጥናት የምክክር መድረክም በዘርፉ ያሉ ዕድሎችን ወደ ጥቅም ለመቀየር ዓላማ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል። 

በኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥነ-ምህዳር ግንባታ፣ የክህሎት ልማት እና አስተምህሮን የሚዳስሱ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም