በአፋር ክልል የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርን በማህበረሰቡ ተሳትፎ ለማጠናከር ጥረት ይደረጋል-- የክልሉ ትምህርት ቢሮ 

235

ሰመራ፣መጋቢት 19/2016 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርን በማህበረሰቡ ተሳትፎ ለማጠናከር ጥረት እንደሚደረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱ ሁሴን ገለጹ።

የቢሮው ከፍተኛ አመራር አባላትና በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ድርጅት የአፋር ክልል አስተባባሪ ፍሎረንስ ላንይሮ በተገኙበት በሚሌ ወረዳ ምገባ የሚካሄድባቸውን ትምህርት ቤቶች ዛሬ ጎብኝተዋል።

አቶ አብዱ በጉብኝቱ ላይ  በክልሉ መርሃ ግብሩ የሚካሄድባቸውን ትምህርት ቤቶች ለማብዛት ዕቅድ መያዙን ገልጸው በመርሃ ግብሩ  ዘንድሮ ከ121 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


 

በዓለም ምግብ ድርጅት 466 ትምህርት ቤቶችን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በክልሉ መንግሥት በተመደበላቸው በጀት መርሃ ግብሩን እያከናወኑ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች መርሃ ግብሩን እያከናወኑ ያሉት ገሚሶቹ ብቻ መሆናቸውንና በቀጣይ በጀት ዓመት መርሃ ግብሩን ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ ይሰራል ብለዋል።

በክልል ደረጃ የምገባ ፈንድ እንዲኖር ስራ መጀመሩን የጠቆሙት ሃላፊው፣ ይህም ዘላቂነት እንዲኖረውና እንዲስፋፋ ማህበረሰብ አቀፍ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በመርሃ ግብሩ የክልሉ መንግሥት በወሰነው መሠረት የአዋሽ ወንዝ በቅርበት በሚገኝባቸው ትምህርት ቤቶች ለግብርና ምቹ የሆነ መሬት ተረክበው ለምገባ የሚያስፈልጋቸውን እንዲያመርቱ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ይህም የምግብ አቅርቦትና አማራጮችን በማስፋት አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት በመፍጠር ተማሪዎች ያለ ስጋት ትምህርታቸውን ለመከታተል ያስችላቸዋል ብለዋል።

መርሃ ግብሩ በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መጠነ ተሳትፎ መጨመሩንና መጠነ ማቋረጥ መቀነሱን ገልጸው፣ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል።

አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስና በድርቅ የሚጎዳ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱ፣ የክልሉ መንግሥትም ችግሩን በመመልከት ለመርሃ ግብሩ የሚመድበውን በጀት እያሳደገ መሆኑን አስረድተዋል። 

ትምህርት ቤቶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኘው ማህበረሰብ ምግብ ማብሰያ የሚሆን ውሃና እንጨት በማቅረብ እንዲሁም ምግብ በማብሰል ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የበከሪ ደአር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሠ መምህር  ሁሴን ሰኢድ፣ በትምህርት ቤቱ በሚካሄደው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎች ቁጥር ጨምሮ 512 መድረሱን ተናግረዋል።

የሚሌ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ አይሻ ናስር በበኩላቸው መርሃ ግብሩ በወረዳው ካሉት 17 መደበኛ ትምህርት ቤቶች በስድስቱ እንደሚካሄድ ገልጸው፣ይህም የመማር ማስተማሩን ሂደት እያነቃቃ ነው ብለዋል።

መርሃ ግብሩ ያልተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች መርሃ ግብሩ እንዲጀመር ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቢሮው ከዓለም ምግብ ድርጅት አፋር ቅርንጫፍ አስተባባሪ ጋር የሚያደርገውን ቅኝት በሌሎችም ትምህርት ቤቶች እንደሚቀጥል ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም