በመዲናዋ ለልማት ከሚኖሩበት አካባቢ የሚነሱ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት መስተጓጎል እንዳይገጥማቸው ዝግጅት ተደርጓል - የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

100

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- በአዲስ አበባ ለኮሪደር ልማትና መልሶ ግንባታ ከሚኖሩበት አካባቢ የሚነሱ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት መስተጓጎል እንዳይገጥማቸው ቀደም ብሎ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ባልተገባ መንገድ የዓመት ክፍያ በጠየቁ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ላይም ቢሮው እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።

በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሥራ በአምስት ኮሪደሮች የተለየና ስድስት ክፍለ ከተሞችን የሚያካልል መሆኑ ይታወቃል።

የኮሪደር ልማት ሥራው ከተማዋን የሚመጥን ሰፊና ዘመናዊ የመሰረተ ልማት አውታር ለመገንባትና የከተማዋን ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ነው።

በዚህም ሰፋፊ መንገድ፣ ወጥ እና ዘመናዊ የመብራት ዝርጋታና ለከተማው ተጨማሪ ውበት የሚሰጡ የመንገድ ዳር የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የሚከናወኑ ይሆናል።

ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት፣ ሰፋፊና ምቹ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ ያረጁ ሕንፃዎች ጥገና፣ የማስዋብና ሌሎችም የልማት ሥራዎችን ያካተተ ነው።

ከኮሪደር ልማትና መልሶ ግንባታ ሥራው ጋር በተገናኘ የተማሪዎች መስተጓጎል እንዳይኖር ምን ዝግጅት ተደርጓል? በሚል ኢዜአ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን አነጋግሯል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ በመልሶ ማልማትና ኮሪደር ልማት ሂደቱ ከሚኖሩበት አካባቢ የሚነሱ ቤተሰብ ልጆች በመማር ማስተማር ሂደቱ ምንም ዓይነት መስተጓጎል እንዳይገጥማቸው ቀደም ብሎ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

አካባቢው ለልማት መፈለጉ ከታወቀ ጊዜ አንስቶ ተማሪዎች የሚሄዱባቸው ቦታዎች ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች መቀበል እንዲችሉ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቶቹ የቅበላ አቅም እንዲያድግ የተለያዩ ሥራዎች ቀደም ብለው ተከናውነዋል ብለዋል።

ለተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች ከትምህርት ማኅበረሰቡ ጋር በትብብር እያከናወኑ መሆኑንም ነው ዶክተር ዘላለም የገለጹት።

በመልሶ ማልማት ከሚኖሩበት አካባቢ ለተነሱ ቤተሰብ ልጆች ዓመታዊ ክፍያ የጠየቁ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ላይም ቢሮው እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ባልተገባ መንገድ የዓመት ክፍያ የተጠየቁ ወላጆች ለትምህርት ቢሮ ጥቆማ መስጠት ይችላሉ ብለዋል።   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም