የመዲናዋን ነዋሪዎች በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

144

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- የመዲናዋን ነዋሪዎች በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለልማት ተነሽዎች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአገር ባለውለታዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የግንባታው መከናወን የበርካቶችን የመኖሪያ ቤት ችግር የሚፈታ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትን ዜጎች ህይወት ለማሻሻል የሚያስችል ነው ብለዋል።

የሚገነቡት ሶስት ሕንፃዎች የግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ በበጎ ፈቃደኛ ባለ ኃብቶች የሚሸፈንና በ90 ቀናት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማ ግብርና፣ የሌማት ትሩፋት፣ የቤቶች ግንባታና ሌሎች ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በቀጣይም የመዲናዋን ነዋሪዎች በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን በማከናወን ረገድ የመንግስትና የባለሃብቶች ቅንጅታዊ ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኛ ባለኃብቶች በበኩላቸው፤ በመዲናዋ እየተከናወኑ ባሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ላይ ተሳትፏቸውን አጠናከረው የሚቀጥሉ መሆኑን ተናገረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም