የፈረንሳይ መንግስት በክልሉ በቱሪዝም፣ በጤናና ሌሎች ልማቶች የሚያደርገው ድጋፍ የሚበረታታ ነው - አቶ አረጋ ከበደ

131

ባህርዳር ፤መጋቢት 19 /2016 (ኢዜአ)፡-የፈረንሳይ መንግስት በአማራ ክልል ለሚካሄዱ የቱሪዝም፣ የጤናና ሌሎች ልማቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

አቶ አረጋ ከበደ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ ጋር በልማትና ድጋፍ ዙሪያ በባህርዳር ከተማ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይም ርዕሰ መስተዳድሩ የፈረንሳይ መንግስት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገናን ጨምሮ ለተለያዩ የልማት ስራዎች እያደረገ ያለውን የትብብር ድጋፍ አመስግነዋል።

በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ለተጎዱ ወገኖች በፈረንሳይ መንግስት እየተደረገ ያለው ሰብአዊ የትብብር ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ በበኩላቸው፤ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ምርጥ ዘር በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ይህም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ቀደም ሲል በቅርስ ጥገና፣ በጤናና ሌሎች የልማት መስኮች ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ ለማስፋት መሆኑንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም