የድምጽ ብክለት በማስከተል ችግር የፈጠሩ 1 ሺህ 164 የተለያዩ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል- የመዲናዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን

187

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- በበጀት ዓመቱ ስምንት  ወራት የድምጽ ብክለት በማስከተል ችግር የፈጠሩ 1 ሺህ 164 የተለያዩ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

የድምጽ ብክለት በሰዎች የጉዞ፣ የእንቅልፍ፣ የስራ፣ የትምህርት፣ የንግግር ወይም በመሳሰሉት መስተጋብር ላይ ስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ጤንነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም ይህንን ችግር ለመከላከል በኢትዮጵያ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995) ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል።

ለመኖሪያ አካባቢዎች፣ ለንግድ አካባቢዎችና ለኢንዱስትሪ ዞኖች መውጣት የሚገባው የድምጽ መጠን በድምፅ ልኬት መሳሪያ ዲሲቢልስ (dB) መሰረት በቀን እና በማታ የተመጠነ አድርጎ አስቀምጧል።

በመሆኑም በሳይንሳዊ ልኬቱ መሰረት ለተጠቀሱት አካባቢዎች በቀን 55፣ 65 እና 75 ዲሲቢል ሲሆን በሌሊት ደግሞ 45፣ 57 እና 70 ዲሲቢልስ እንዳይበልጥ ያስገድዳል።

ከዚህ ካለፈ ግን የድምጽ ብክለት የሚፈጥር በመሆኑ ማህበራዊ ችግር የሚያስከትል መሆኑ ይነገራል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ዲዳ ዲሪባ፤ የተቀመጠውን ህግ በሚተላለፉ ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በ1 ሺህ 164 በሚሆኑ ተቋማት ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ የገንዘብ ቅጣትና የመስሪያ ቦታ ማሸግን ያካተተ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል። 

እርምጃው ከተወሰደባቸው መካከል በርካቶቹ ከህብረተሰቡ የድምጽ ብክለት አቤቱታዎችን መነሻ በማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሰራሩ መሰረት ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በንግድና በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ባለስልጣኑ ባወጣው የድምጽ ልኬት መሰረት ሕግና ደንብ አክብረው እንዲሰሩ አሳስበው ተላልፈው በሚገኙት ላይ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ አሳስበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም