ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 15 ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል- የመዲናዋ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ

160

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- ለዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 15 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመከላከልና የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ደግሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና እንዳለው ይታመናል።

በዚህም መሰረት ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በመዲናዋም ዘንድሮ ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገልጿል።


 

የቢሮው የችግኝ ጣቢያ የግብአት አቅርቦት ስርጭት ቡድን መሪ ጌትነት አድማሱ፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት በዘጠኝ የችግኝ ጣቢያዎች የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች የማፍላት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

በዚህም ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 15 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። 


 

በቢሮው የእንጦጦ ችግኝ ጣቢያ ተቆጣጣሪ ወጣት በረከት መርጋ፤ የሶስኒ የችግኝ ጣቢያ ተቆጣጣሪ ወይዘሪት አበበች መካ ለክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ችግኝችን በብዛትና በአይነት የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በመዲናዋ ለሚከናወነው የክረምት የችግኝ ተከላ የተለያዩ አይነት ዝርያ ያላቸውን ችግኞች ለማቅረብ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።


 

2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም በአራት ዙሮች በተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

በሁለተኛው ምእራፍ የመጀመሪያ ዓመትም (በ2015 ዓ.ም) 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም