የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ከከተማ ልማትም ባለፈ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ የነበሩ ዜጎችን የታደገ ነው

178

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):-  የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ከከተማ ልማትም ባለፈ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ የነበሩ ዜጎችን የታደገ መሆኑን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድሞ የመከላከል እና ከተከሰተም ፈጣን ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

በኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ይክፈለው ወልደመስቀል፤ የእሳት ቃጠሎ፣ የመኪና አደጋ፣ የግንባታ መደርመስ፣ የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ በመዲናዋ ከሚከሰቱ አደጋዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ የቤቶች ግንባታ ጥግግት፣ የመንገዶች ጥበት፣ የኤሌክትሪክ ማስተለለፊያ ገመዶች መደራረብ እና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች መደፈን በምክንያትነት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት በመዲናዋ በተለያዩ አደጋዎች የ31 ሰዎች ህይዎት ማለፉንና 467 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ኮሪደር ልማት ከከተማ ልማትም ባለፈ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ የነበሩ ዜጎችን ከችግር የታደገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ እና የመልሶ ግንባታ ስራው የአዲስ አበባን ገጽታ የሚያሳምርና የሚያጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የኮሪደር ልማት መርሃ ግብሩ ቤቶች በፕላን እንዲገነቡ፣ መንገዶች እንዲሰፉ፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በጥራት እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በርካታ አካባቢዎችን ከእሳት ቃጠሎ፣ ከጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ከትራፊክ መጨናነቅና ሌሎችም አደጋዎች የታደገ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባ ከተማን ታላቅነት የሚመጥን ስራ ለመስራትና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመረ የመልሶ ግንባታ ስራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም