ፈቃድ ያልተሰጣቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶችን ይዘው በተገኙ 90 የሕክምና ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል--የክልሉ ጤና ቢሮ

61

ቦንጋ ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ)፡- እንደ ሀገር ፈቃድ ያልተሰጣቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶችን ይዘው በተገኙ 90 የሕክምና ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ በመንግስትና በተለያዩ ፕሮግራሞች አማካኝነት በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር  ባለሥልጣን እውቅና ተሰጥቷቸው በርካታ መድሀኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ።

ይሁንና ፈቃድ ያልተሰጣቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም ከመንግስት ውጭ በግል የጤና ተቋማት መገኘት የሌለባቸው መድሀኒቶች በህገወጥ መንገድ ለህብረተሰቡ በወድ ዋጋ ሲሸጡ ይስተዋላል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ እንዳሉት፣ በክልሉ የሚስተዋለው ህገወጥ የመድሃኒት ዝውውርና ስርቆት ከአቅርቦት ውስንነት ጋር ተዳምሮ በዘርፉ ላይ ጫና እያሳደረ ነው። 

ቢሮው ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ ባደረገው ቁጥጥር በክልሉ 90 የግል ሕክምና ተቋማት በሀገር ደረጃ ያልተመዘገቡና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶችን ይዘው በመገኘታቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

"ከእነዚህ ውስጥ 30ዎቹ ፍቃዳቸው የተሰረዘ ሲሆን ቀሪዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እርምጃ የተወሰደባቸው ናቸው" ብለዋል።

በመንግስት የጤና ተቋማት ብቻ መገኘት ያለባቸውን መድሀኒቶች በህገ ወጥ በሆነ መንገድ ለግል ጤና ተቋማት በሸጡ ባለሙያዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ ለመውሰድ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ሀይሌ ገልጸዋል።

ይህ ድርጊት በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ የሚያስከትለው ኢኮኖሚዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ የተጀመረው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት የመድሀኒት አስተዳደር ስርዓትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አቶ ሀይሌ ገልጸው፣ "የጤና ተቋማትና የጤና መድህን ቦርድን ለማደራጀት እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።

በክልሉ የምዕራብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሺማጂ ቁርጡሚ፣ ችግሩ በዞኑ በሰፊው እየተስተዋለ መሆኑን ተናግረው፣ ችግሩ በህብረተሰቡ ላይ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል ብለዋል።

"በዞኑ 20 የግል የጤና ተቋማት ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 11ዱ በግል ጤና ተቋማት መያዝ የሌለባቸው መድሃኒቶችን ይዘው ተገኝተዋል" ብለዋል። 

የወባ፣ የቲቢ፣ ቫይታሚን-"A"፣ ፕላንፕሌት እና ሌሎች በግል ጤና ተቋማት መገኘት የሌለባቸውን ይዘው የተገኙ የጤና ተቋማትም ፍቃዳቸው መሰረዙን ገልጸዋል።

መድሀኒቶቹን ከመንግስት ተቋማት በህገወጥ መንገድ ያወጡ ሠራተኞችን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንና በድርጊቱ በተሳተፉ ተቋማት ላይም እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት በከፋ ዞን 16 መድሃኒት መደብሮች እና 4 ማከፋፈያዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በድርጊቱ የተሳተፉ የጤና ተቋማት መገኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ ናቸው።

ይህን ህገወጥ ተግባር ለመከላከል ክትትልና ድንገተኛ ፍተሻውን ከማጠናከር ባለፈ በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይቀጥላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም