የዞኑ አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው

98

አዳማ፤መጋቢት 19/2016 (ኢዜአ)፡-የምስራቅ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ትኩረት በመስጠት ምርታማነታቸውን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት ቡድን መሪ አቶ ከፍያለው ለማ፣ አርሶ አደሩ ከሰብል ምርት ባሻገር አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ገቢውን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአስር ሺህ በላይ የዞኑ አርሶ አደሮችም በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ በመሰማራት በዓመት ከ400 ሺህ ብር በላይ ገቢ በግለሰብ ደረጃ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በዚህ ዓመት ከ5 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በ11 አይነት የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶች መሸፈኑንና በአመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በዞኑ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

በዞኑ ያለው ለም መሬትና የውሃ ሃብት እንዲሁም ለማዕከላዊ ገበያ ቅርብ መሆኑ በአትክልትና ፍራፍሬ ረገድ በርካታ ስራዎች እንዲሰሩ እድል መፍጠሩን አቶ ከፍያለው ተናግረዋል።

ከፈንታሌና መተሃራ ዝቅተኛ አካባቢዎች እስከ ጉምቢቹ ከፍተኛ ቦታዎች ድረስ በዞኑ 11 ወረዳዎች የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶች እየለሙም ይገኛሉ፡፡


 

በቆላማው ወረዳዎች ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ፓፓያ ሲለማ በስምጥ ሸለቆዎች ደግሞ አቮካዶ እንዲሁም ደጋ ላይ አፕልና እና ዘይቱና በክላስተር እየተመረተ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የተሰማሩ ውጤታማ የዞኑ አርሶ አደሮች ከግብርና ባለሙያዎች በሚደረግላቸው የግንዛቤና የግብአት ድጋፍ ታግዘው ሀብት ማፍራት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡


 

አርሶ አደር ቱፋ አለሙ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካንና ሸንኮራ በማምረት የገቢ ምንጫቸውን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

ከአንድ ጊዜ ምርት ከ400 ሺህ ብር በላይ እንደሚያገኙ ጠቁመው በተለይ የአቮካዶን የምርት ጥራት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግርዋል፡፡

አርሶ አደር ከበደ ቱሉ በበኩላቸው ከሶስት ዓመታት በፊት ጀምሮ አቮካዶን በስፋትና በጥራት በማምረት ለሌሎች አርሶ አደሮች ጭምር ልምዳቸውን በማካፈል ለስራ አጦችም የስራ እድል በመፍጠር ጭምር ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡     

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም