በግንባታ ላይ ያሉ በጊዜያዊነት ዝግ የሆኑ መንገዶች እና አማራጭ መንገዶች ይፋ ሆኑ

91

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- በግንባታ ላይ ያሉ በጊዜያዊነት ዝግ የሆኑ መንገዶች እና አማራጭ መንገዶች ይፋ ሆኑ።

ከ4 ኪሎ እስከ ፒያሳ ባለው መስመር የራስ መኮንን ድልድይ እየተሰራ በመሆኑ፤ የመንገድ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ፍጹም መቆም የሚከለክሉ የትራፊክ ምልክቶች እየተተከሉ መሆኑ ተገልጿል።

እስከአሁን ባለው ሂደት በተለይም በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት በአካባቢው ላይ በመንገድ መዘጋጋት ህብረተሰቡ እንዳይጉላላ፤ አሽከርካሪዎች ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ለትራፊክ ፖሊስ አባላት እና ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቁጥጥር ሰራተኞች ትዕዛዝ ተባባሪ እንዲሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በአካባቢው በስፋት ሲሰጥ መቆየቱ ተጠቁሟል።

በዚሁ መሰረት ፍጹም መቆም የሚከለክሉ ምልክት የተተከለባቸው፤ ከቴዎድሮስ አደባባይ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስድ ዋና መንገድ እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ እንዲሁም ማዘጋጃ ዙሪያ ከዛሬ ጀምሮ ጥብቅ ቁጥጥር ይጀመራል ተብሏል።

በአካባቢው ላይ በጊዜያዊነት ለተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የሚውል የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሰርፌስ ፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት ስለጀመረ አሽከርካሪዎች እንደ አማራጭ መጠቀም እንደሚችሉ ተገልጿል።

* ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ደጎል አደባባይ

* ከአራት ኪሎ ወደ ራስ መኮንን ድልድይ፣ አማራጭ መንገድ ከአራት ኪሎ-አባድር

* ከደጎል አደባባይ ትራፊክ መብራት ወደ 4 ኪሎ

* ከአራዳ ክፍለ ከተማ 4 ኪሎ አደባባይ

* ከቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ራስ መኮንን ድልድይ

* ከደጃች ውቤ ወደ ራስ መኮንን ድልድይ

* ከአፍንጮ በር ወደ ራስ መኮንን ድልድይ

* ከባሻወልዴ ችሎት ወደ ራስ መኮንን ድልድይ እና ከቀበና ወደ ፒያሳ የሚመጡ አሽከርካሪዎች መንገዱ ግንባታ ላይ መሆኑን ተገንዝበው ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ተገልጿል።

አሽከርካሪዎች ለትራፊክ ፖሊስ አባላት እና የቁጥጥር ሰራተኞች ትዕዛዝ እንደወትሮው ተባባሪ እንዲሆኑም ተጠይቋል።

በአካባቢው ያለውን የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ለመቅረፍ፤ አማራጭ ማስተንፈሻ የሚሆን መንገድ በተለምዶ ስሙ ከቀይባሕር ኮንደሚንየም ወደ ደጎል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ዛሬ ከሰዓት ለተሽከርካሪዎች ክፍት እንደሚሆን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም