በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አገራት በመደመር እሳቤ በትብብር ሊሰሩ ይገባል

205

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):-  በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሀገራት በመደመር እሳቤ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የፓናል ውይይት "ቀጣናዊ ሰላም እና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው። 


 

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ "ቀጣናዊ ትስስር እና የህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት" በሚል ርዕሰ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የተለያዩ መልክዓ ምድሮች ፣ ባህል እና ታሪካዊ ዳራ ያለው እንዲሁም የሃያላን ሀገራት የትኩረት ማዕከል መሆኑን በፅሁፋቸው አንስተዋል።

ቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው የቀይ ባህር እና የገልፍ ኦፍ ኤደን መገኛ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።


 

በሌላ መልኩም ቀጣናው ለጠንካራ አብሮነት እና ሰላም ግንባታ ምቹ የሆነ አካባቢ መሆኑን አንስተው ለመሰረተ ልማትና ለጋራ ተጠቃሚነት ምቹ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣናው ሽብርተኝነት ስጋት፣ ያልተረጋጋ ፖለቲካ ስርዓት እና የድንበር ላይ ግጭቶች ፈተናዎች ስለመሆናቸውም አብራርተዋል።

በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሀገራት በመደመር እሳቤ በትብብር ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በቀጣናው የልማት ትስስርና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው የድንበር ላይ ንግድን ለማጠናከር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም