በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ሀብት ማሰባሰቢያ የቦንድ ሳምንት ህዝባዊ ንቅናቄ እንደሚካሄድ ተገለጸ

87

አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሀብት ማሰባሰቢያ የቦንድ ሳምንት ህዝባዊ ንቅናቄ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

"በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ አሰባሰብ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ  ላይ በአርባምንጭ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው ።


 

በክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት  ሃላፊ አቶ ሚልኪያስ እስራኤል በወቅቱ እንዳሉት፤  ከክልሉ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ እንደቀጠለ ነው።

በተያዘው የበጀት ዓመት  ስምንት ወራት በተደረገው እንቅስቃሴም ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዬን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ገልጸዋል። 

ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ እንደሚጠናከር በማመልከት አስተዋጽኦ  ላደረጉና እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የግድቡ ግንባታ 13ኛ ዓመት በማስመልከት ከዛሬ ጀምሮ የቦንድ ሳምንትና የድጋፍ ማሰባሰቢያ ህዝባዊ ንቅናቄ እንደሚካሄድ አቶ ሚልኪያስ አስታውቀዋል።

እየተገባደደ ላለው የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንደቀደመው ሁሉ በቀጣይም ቦንድ በመግዛትና በ8100 A ጭምር ነዋሪዎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውይይት መድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም አሁን ላይ 95 በመቶ መድረሱን ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም