ኢትዮጵያ በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኗ ተገለጸ

195

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ አመታት በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኗን የህግ፣የሰላምና ልማት ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሰላም ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር በመተባበር የተዘጋጀው "ቀጣናዊ ሰላም እና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር" በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ፍስሐ ይታገሱ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የህግ፣ የሰላምና ልማት ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ "ቀጣናዊ ትስስር እና የህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት" በሚል ርእስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ አመታት በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኗን ጠቅሰዋል።

የተለያዩ አገራት የትስስር ሂደቶች እና የትስስር ደረጃዎችን በማብራራት የትስስር መጠናከር መተማመን እና መረጋጋት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ስጋት እና ተስፋ በእኩል የሚስተናገዱበት መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ የተከተለ የልማት ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።

ከቀጣናው ባለፈ አህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ቀጣናውን በማስተሳሰር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣናዊ የንግድ ትስስር፣ መሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት እና በሃይል ልማት ተጨባጭ የልማት ስራዎችን ኢትዮጵያ እያከናወነች መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም