ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ የልማትና የንግድ ትስስር ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል 

227

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ የተከተለ የጋራ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና የንግድ ትስስር ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ።

"ቀጣናዊ ሰላም እና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት በኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ እየተካሄደ ነው። 

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም፤ በኢትዮጵያ ልማትን ለማፋጠንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጋራ ልማት ባሻገር የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ለመጠበቅና ዘላቂ ለማድረግ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

አለመግባባትና ግጭቶች በነበሩባቸው አካባቢዎች አሁን ላይ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን አስታውሰው ለዚህም ህብረተሰቡ ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በመንግስት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው የሁሉም አካላት እገዛ እንዲታከልበት ጠይቀዋል።

በመንግስት በኩል ማናቸውንም ችግሮች በውይይት የመፍታት የጸና አቋም መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ ከግጭት ጉዳት እንጂ አንድም ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ለሀገር ጠቃሚውና ማንንም አትራፊ ማድረግ የሚችለው የሰላምና የውይይት አማራጭ ብቻ መሆኑን አጽኖት ሰጥተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የሚታየውን የሽብር፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለመግታት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።


 

ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በብዙ ችግሮች የሚፈተን መሆኑን ያነሱት አቶ ብናልፍ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በመስራት ቀጣናዊ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል:: 

ቀጣናዊ ሰላምን ማረጋገጥ የብዙ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸው በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከተለያዩ የቀጣናው ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጀመሩት ትስስር በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህንን አይነት ተሞክሮዎችን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባ ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር እና የሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ተልኮውን ለመወጣት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መድረኮችን በማዘጋጀትም በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ዜጎች የጋራ ምልከታ እንዲኖራቸው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም ዜጎች ለጋራ ጥቅም በጋራ እንዲቆሙ የሚያደርጉ መድረኮችን በማዘጋጀት ሀገራዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከዚህ ቀደም በርካታ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው መድረኮች ሲያዘጋጅ መቆየቱ ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም